አሜሪካ ከመቼውም ጊዜ በላይ ደንግጣለች። ኦባንግ እንዳሉት ለህዝባቸው “ሬት” ለምዕራባውያንና “ማር” (የቤት ቀጋ፤ የውጭ አልጋ) የነበሩት አምባገነን በድንገት እንደ ተነቀለ ቡሽ ተስፈንጥረው ከሲስተም መውጣታቸው አሜሪካንን አስጨንቋታል። በተለይም እሳቸው አፍነው የያዙት የስርዓቱ “ክፉ ጠረን” አሁን እነርሱ (አሜሪካውያኑ) ደጅ የደረሰ ያህል መፍትሄ ለመፈለግ የወሰኑ ይመስላሉ። አውቀውና ፈቅደው ሲታለሉ የቆዩበትን ጊዜ አስልተው መንገዳቸውን የማስተካከል ስራ የጀመሩት ዛሬ አይደለም። [...]
↧